አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩዋንዳ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሙባረክ ሙጋጋ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ሲሳይ ቶላ በአካባቢያዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት ውይይት አድርገዋል።
አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ ጀኔራል ሙባረክ ሙጋጋ እና አቶ ሲሳይ ቶላ በሁለቱ ሀገራት በአካባቢው ፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም በሀገራቱ ወታደራዊ እና የደኅንነት አቅም ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መክረዋል።
በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የተከናወኑት የሪፎርም ትግበራ ሂደት የሚያሳየውን የተቋሙን ኢንተለጀንስ ፊውሽን ሴንተር እና የዲጂታል ኢግዚቢሽን የጎበኙት ጀኔራል ሙባረክ ሙጋጋ፤ አገልግሎቱ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና ተቋማዊ አሰራር የሪፎርም ሥራዎች ተከትሎ ያስመዘገባቸው ውጤቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያስችል ከፍ ያለ አቅምና ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማስቻሉን በሠጡት አስተያያት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት የተመረቀውንና የሲቪል፣ ወታደራዊና የደኅንነት አገልግሎት የሚሠጡ ድሮኖችን ለማምረት የተቋቋመውን የስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ የድሮን ማምረቻ ፋብሪካ ተዘዋውረው በመጎብኘት፤ ኢትዮጵያ በወታደራዊና ደኅንነት ዘርፍ በደረሰችበት ልህቀት መደነቃቸውን አያይዘው ተናግረዋል።