አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ደሴ ከተማ ከአንድ ሺህ በላይ የክላሽንኮቭ ጥይት በመገበያየት የተጠረጠሩ ሦስት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዋና ክፍል ባለሙያ ኢንስፔክተር ተስፋዬ ከበደ እንደገለጹት፤ ተጠርጣሪዎቹ ዛሬ በደሴ ከተማ የተያዙት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ፖሊስ ባደረገው ጥብቅ ክትትል ነው።
በዚህም ተጠርጣሪዎቹ ከ1 ሺህ በላይ የክላሽንኮቭ ጥይት ሲገበያዩ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ጉዳዩን በማጣራትና በመመርመር ተጠርጣሪዎችን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በዞኑ ሰላምን ለማጽናት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ኢንስፔክተር ተስፋዬ ገልጸዋል።