Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሶማሌ ክልል የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሶማሌ ክልል የአርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የኮለንና ሀሮዋ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አብዱላሂ ሀሰን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷በክልሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማልማት የአርብቶ አደሩን ሕይወት የሚቀይር ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡

አርብቶ አደሩ ከፊል አርሶ አደር እንዲሆን የማሳያና የእገዛ ሥራ በመስራት የተሻለ ውጤት መምጣቱን ጠቁመው ÷ለአብነትም በሲቲ ዞን ኮለንና ሀሮዋ 1 ሺህ 442 ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን አንስተዋል።

ከ1 ሺህ 442ቱ ሄክታሩ 1 ሺህ 228 የሚሆነው በሽንኩርት የለማ ሲሆን÷ ቀሪው ደግሞ በሃባብ እና ሌሎች አትክልቶች መሸፈኑን ገልጸዋል።

በዞኑ 848 አባዎራዎችን ከፊል አርብቶ አደር ማድረግ መቻሉን ጠቁመው÷በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት አርብቶ አደሩን ወደ ዘመናዊ የመስኖ ልማት ሥራ ለማሸጋገር 42 የውሃ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን ገልጸዋል፡፡

ለውሃ ጉድጓዶቹም የውሃ ፓንፕ ገጠማ ሙከራ እና የመስመር ዝርጋታ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው ሥራ አስኪያጁ ያብራሩት ።

በታሪኩ ለገሰ

Exit mobile version