ቢዝነስ

ኢትዮጵያ እና እስራኤል ትብብራቸውን በይበልጥ ለማሳደግ ያለመ ምክክር አደረጉ

By ዮሐንስ ደርበው

March 14, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከእስራኤል የኢነርጂ እና የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን ጋር በሁለትዮሽ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም፤ በኃይል፣ በመሠረተ ልማት፣ በማዕድን እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች የሀገራቱን የሁለትዮሽ ትብብር ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

ተጨባጭ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት ለመፍጠር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) አረጋግጠዋል፡፡

ለዚህም እየተተገበረ ያለው የኢኮኖሚያዊ ማሻሻያ የእስራኤል ኢንተርፕራይዞችን ጨምሮ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኃይል ዐቅም እና በአፍሪካ እያደገ በመጣው የኃይል ገበያ ሁለቱም ወገኖች ተጠቀሚ እንዲሆኑ፤ የእስራኤል ኩባንያዎች በታዳሽ ኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ እና ሥርጭት ፕሮጀክቶች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀርበዋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተትረፈረፈ እና በሚጠበቀው ልክ ጥቅም ላይ ያልዋለ የማዕድን ሀብት መኖሩን ጠቁመው፤ በዘርፉ መሠማራት በሚችሉበት አግባብ ላይ ተወያይተዋል፡፡

እንዲሁም በግብርና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሀገራቱን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ እና በእስራኤል መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ያረጋገጡት ሚኒስትር ኮኸን በበኩላቸው፤ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በይበልጥ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የእስራኤል ኩባንያዎች በዘርፉ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያርጉ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ፤ የቢዝነስ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ጠቁመዋል፡፡