የሀገር ውስጥ ዜና

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በይበልጥ የክልሉን ኢኮኖሚ ማገዝ እንዳለባቸው ተመላከተ

By ዮሐንስ ደርበው

March 12, 2025

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ምርታማነታቸውን በይበልጥ ማሳደግና የክልሉን ኢኮኖሚ ማገዝ እንዳለባቸው ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡

የክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የ2017 በጀት ዓመት የሰባት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡

ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የልማት ድርጅቶቹ አዳዲስ አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ማሳደግና የክልሉን ኢኮኖሚ ማገዝ አለባቸው፡፡

የክልሉን የገቢ ዐቅም በማሳደግ የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ወራት ክልሉ በችግር ውስጥ ሆኖም አብዛኞቹ የልማት ድርጅቶች ጠንክረው በመሥራታቸው ትርፋማና ስኬታማ ሆነዋል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በቀጣይም አሁን ያስመዘገቡትን ትርፍ በማሳደግ የክልሉን ልማት በይበልጥ ለማፋጠን ጠንክረው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡