አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት አሜሪካ በፈረንጆቹ 2026 ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት እንደምትወጣ አረጋግጧል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ጤና ድርጅት የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ምክትል ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ ተቋሙ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ደብዳቤ እንደደረሰው ገልጸው፤ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት በሚቀጥለው ዓመት የምትወጣ መሆኗን ይፋ አድርገዋል።
ሃቅ አሜሪካ ከአባልነት እንደምትለቅ የሚገልጽ ደብዳቤ መጻፏን አረጋግጠዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትን በገንዘብ በመደገፍ ቀዳሚ የሆነችው አሜሪካ በ2024/25 የበጀት ወቅት 261 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡
ይህም ድርጅቱ ከሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ 18 በመቶውን የሚሸፍን መሆኑን አል-ጀዚራ ዘግቧል።
የአሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት መልቀቅ ለተቋሙ ከፍተኛ ጉዳት መሆኑ የተነገረ ሲሆን በተለይም ኤችአይቪ/ኤድስን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል ለሚያደርገው ጥረት አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።