የሀገር ውስጥ ዜና

በእሳት እና በመኪና አደጋ የ13 ሰዎች ህይወት አለፈ

By Feven Bishaw

January 23, 2025

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደብረ ብርሀን ከተማ በደረሰ የእሳት እንዲሁም በሐረር ከተማ እና በስልጤ ዞን በደረሰ የትራፊክ አደጋ በአጠቃላይ የ13 ሰዎች ህይወት አለፈ።

በስልጤ ዞን ሁልባራግ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ8 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ አደጋው ዛሬ ከጠዋቱ 3፡30 በወረዳው ሌፎ በሚባል አካባቢ ከአዲስ አበባ ወደ አርባ ምንጭ ይጓዝ የነበረ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ከባጃጅ ጋር በመጋጨቱ አደጋው ደርሷል።

በአደጋው የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል የወረዳው መረጃ ያመላክታል፡፡

የእሳት አደጋው በደብረብርሀን ከተማ ባህርሀይል ቀበሌ ትናንት ምሽት 2፡30 የደረሰ ሲሆን የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሶስት ሰዎች ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ በአንድ ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ የትራፊክና መረጃ ክፍል ሀላፊ ኮማንደር ኪዳኔ በቀለ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ የእሳት አደጋው የተነሳው ከመኖሪያ ቤት መሆኑንና በቤት ውስጥ ቤንዚን መኖሩ አደጋውን አባብሶ ለመቆጣጠር አዳጋች እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡

በእሳት አደጋው ጉዳት የደረሰበት አንድ ግለሰብ በደብረ ብርሀን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ህክምናውን እየተከታተለ መሆኑ መገለጹን ሪፖርተራችን አላዩ ገረመው ዘግቧል።

በሌላ በኩል በሐረር ከተማ ዛሬ ሌሊት 8፡00 ሰዓት ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ጣሰው ቻለው እንደገለጹት፤ አደጋው የደረሰው በሬ የጫነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪን ለማዳን ሲሞክር በመገልበጡ ነው፡፡

በአደጋውም በአይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ የነበሩ ሁለት ሰዎች ህይወት ወዲያው ሲያልፍ በአንድ ሰው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱንና በአይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ ከተጫኑት 15 በሬዎች መካከልም ሶስቱ መሞታቸውንም ገልጸዋል።

የአይሱዙ አሽከርካሪው ለጊዜው መሰወሩን ጠቁመው፤ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።