አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተመጣጣኝ ዋጋ ለአውሮፓ ሀገራት የሚቀርበው የሩሲያ ጋዝ መቋረጥ የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ሲሉ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ገለጹ፡፡
በስዊዘርላንድ ዳቮስ በተካሄደው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ንግግር ያደረጉት ቮን ዴር ሌየን፥ የአውሮፓ ህብረት ከፈረንጆቹ 2022 በፊት 45 በመቶ ጋዝ እና 50 በመቶ የድንጋይ ከሰል ከሩሲያ ይሸምት ነበር ብለዋል፡፡
በዚህም ሞስኮ ከህብረቱ ከፍተኛ የሃይል አቅራቢዎች ውስጥ አንዷ እንደነበረች አስታውሰው፥ ይህ የሃይል አቅርቦት መቋረጡ አባል ሃገራቱን ጫና ውስጥ መክተቱን ተናግረዋል።
የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ሞስኮ የጋዝ አቅርቦቷን ነፍጋናለች በማለት ጠቅሰው፤ በዚህም ከሩሲያ ወደ ህብረቱ ሀገራት የሚገባው ጋዝ በ75 በመቶ ቀንሷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከሩሲያ ወደ አውሮፓ ጋዝ ሶስት በመቶ ብቻ እንደሚገባ እና የድንጋይ ከሰል ሙሉ ለሙሉ እንደማይገባ ገልጸው፤ በዚህም ሩሲያ የሃይል አቅርቦቷን ማቋረጧ የአውሮፓ ህብረት ሀገራትን የኃይል ቀውስ ውስጥ መክተቱን አልደበቁም፡፡
የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ በኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በኃይል አቅርቦትና በፋይናንስ ዘርፎች ላይ ያነጣጠረ ከፍተኛ የሚባለውን ማዕቀብ መጣሉ ይታወቃል።
በፈረንጆቹ 2022 ሩሲያ በኖርድ ማስተላለፊያ 1 መስመር በኩል ወደ ጀርመን የሚተላለፈውን የጋዝ አቅርቦት አቋርጣ ነበር፤ ይህም በጥገና እና በምዕራቡ ዓለም የተሰሩ መሳሪያዎችን በማቅረቡ ችግሮች ምክንያት እንደነበር የሚታወስ ነው።
በተመሳሳይ ዓመት በባልቲክ ባህር ውስጥ የሚገኙት ሁለት የኖርድ ማስተላለፊያዎች የተመቱ ሲሆን፥ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን የወሰደ ባይኖርም ሞስኮ ከጀርባው የአሜሪካ እና እንግሊዝ እጅ አለበት ብላ ስትከስ ሀገራቱ ድርጊቱን አልፈጸምንም ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
ቮን ደር ሌየን በፎረሙ ላይ የአውሮፓ ህብረት ከሩሲያ ሲቀርብ የነበረውን ኃይል በታዳሽ እና በኒውክሌር ኃይል ሊተካ ይችላል ያሉ ሲሆን፥ ፊታችን ወደታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂዎች በማዞር ኢንቨስት ማድረግ አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
በመሰረት አወቀ