አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ርዕደ መሬት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመሠረተ-ልማት፣ የጊዜያዊ መጠለያ፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የሳይንሳዊ ትንተና እና ትንበያ ቡድኖችን በማደራጀት በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ የርዕደ መሬት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዝግጁነታችንና የምላሽ ሁኔታችን ባለን ቴክኖሎጂ፣ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ትንተናና የትንበያ አቅም የሚወሰን ነው ብለዋል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ የስፔስ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ጉብኝት ማድረጋቸውንና በርዕደ መሬት ነክ ሳይንሳዊ ምርምር አበረታች ስራዎችን ማየታቸውን ገልፀዋል፡፡
“ባለፈው ሳምንት ባካሄድነው የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በርዕደ መሬት ክስተት ዙሪያ ባስቀመጥነው አቅጣጫ መሰረት ወደ ተጠናከረ ተግባር ተገብቷል” ሲሉም ገልፀዋል፡፡
አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች የመሠረተ-ልማት፣ የጊዜያዊ መጠለያ፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የሳይንሳዊ ትንተና እና ትንበያ ቡድኖችን በማደራጀት በዕቅድ ላይ የተመሰረተ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።
መንግሥት የአጭርና የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ዝግጁነትን ለማጎልበት የጥናትና ምርምር ተቋማት ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂና ብቁ የሰው ኃይል ጠንካራ ቁመና እንዲፈጥሩ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡