አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ከኢትዮጵያዊነት እሴት ያፈነገጡ ምስሎችን ለመከላከል የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታወቀ።
ከባህልና እሴት ያፈነገጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እና ፎቶዎች በቲክቶክ፣ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ኢንስታግራም እና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨታቸው እየተስፋፋ መምጣቱ ተገልጿል።
እነዚህ ምስሎች በህፃናት እና ታዳጊዎች እንዲሁም በወጣቱ ትውልድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ምስሎች የሚያስከትሉትን ጫና ለመከላከልና ለመቀነስ በፖሊሲ የተደገፈ ተግባር ለማከናወን የሚያስችል ጥናት መደረጉን የኢመደአ የህግ አማካሪ ፍቅረሥላሴ ጌታቸው ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
ጥናቱን መሰረት በማድረግም የፖሊሲ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ፖሊሲው ከባህልና እሴት ያፈነገጡ ምስሎችን ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ለማገድ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚያስች ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ጥላቻ ንግግር፣ መገለልና መድሎን የሚያንጸባርቁ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በሚያሰራጩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ አመላክተዋል፡፡
ግለሰቦች ወይም የማህበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ጉዳዩን ወደ ህግ በመወሰድ እንደ ፈፀሙት የወንጀል አይነት በገንዘብ እና በእስር እንደሚቀጡም አስገንዝበዋል።
ኢመደአ የሳይበር ምህዳሩን ደህንነትን ለመጠበቅ በርካታ ስራዎችን እያከነወነ እንደሚገኝም የህግ አማካሪው ጠቅሰዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ