አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዘዞ-ጎንደር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በቅርቡ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል፡፡
በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ እየተከናወነ የሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክቱ ÷ከዚህ ቀደም በሌላ የሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ አማካኝነት ግንባታው ሲከናወን ቆይቶ ከአፈጻጸም ውስንነት ጋር በተያያዘ ውሉ መቋረጡ ይታወሳል፡፡
12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነውን ፕሮጀክት ቀሪ ሥራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንዲቻል በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጎንደር መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ግንባታውን ተረክቦ እየሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
21 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ በመገንባት ላይ የሚገኘው ፕሮጀክቱ አብዛኛው የስትራክቸርና ተጨማሪ ዋና ዋና የፕሮጀክቱ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል ተብሏል፡፡
አሁን ላይ የአስፋልት ማንጠፍ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመላክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመንገዱ የቀኝ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ አስፋልት የማንጠፍ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን÷የግራው አቅጣጫ ደግሞ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ሲቀር የአስፋልት ንጣፍ እንደተደረገለት ተጠቅሷል፡፡
የመንገዱ የግንባታ ሂደት በመዘግየቱ ነዋሪዎች ለትራንስፖርት መስተጓጎል ችግር ሲዳረጉ እንደነበር የገለጸው አስተዳደሩ÷አሁን ላይ የግንባታ ሒደቱ እየተፋጠነ በመሆኑ ችግሩ እየተቀረፈ ነው ብሏል፡፡
ዲስትሪክቱ አሁን ላይ ከፕሮጀክቱ በተጨማሪ 700 ሜትር የጎንደር ከተማ አስፋልት ሥራና ሌሎች ተጨማሪ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡