አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሕንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰው አልባ የጠፈር መንኮራኩሯን ለመጀመሪያ ጊዜ ህዋ ላይ በማኖር አራተኛ ሀገር መሆኗ ተሰምቷል፡፡
ይህ የሕንድ ስኬት ለወደፊት ተልዕኮዎቿ ቁልፍ ሚና አለውም ተብሎለታል፡፡
መንኮራኩራቸውን ህዋ ላይ በማኖር የሚጠቀሱት ሀገራት ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ቻይና ሲሆኑ፥ በዛሬው ዕለት ሕንድ ሀገራቱን በመቀላቀል አራተኛዋ ሆናለች።
በዚህም የሕንድ የጠፈር ምርምር ድርጅት ቀኑን “ታሪካዊ” ሲል ጠርቶታል፡፡
የሕንድ የጠፈር ኤጀንሲ ተልዕኮ እንዳለው፥ የጠፈር መንኮራኩርን ሕዋ ላይ የማኖር ሙከራ (ስፓዴክስ) እያንዳንዳቸው 220 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ሁለት ትናንሽ መንኮራኩሮችን ወደ ዝቅተኛ የምድር ምህዋር በማሰማራት የተደረገ ነው፡፡
“ታርጌት“ እና “ቼዘር“ የተባሉት መንኮራኩሮቹ ከሁለት ሣምንት በፊት በሕንድ ሰራሽ ሮኬት በደቡባዊ አንድራ ፕራዴሽ ግዛት በሚገኘው የሳቲሽ ዳዋን የጠፈር ማዕከል ተወንጭፈዋል ነው የተባለው፡፡
በዚህም የሀገሪቱን ስኬት አስመልክተው የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በመልዕክታቸው ተመራማሪዎቻችንና ይህ እንዲሳካ ስትጥሩ የነበራችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
አክለውም ይህ ስኬት ለመጪዎቹ የሕንድ ትላልቅ የጠፈር ተልዕኮዎች ወሳኝ መሰረት ነው ማለታቸውን ጠቅሶ የዘገበው ሲኤንኤን ነው፡፡
ቴክኖሎጂው ሀገሪቱ ቁሳቁሶችን ከአንዱ ሳተላይት ወይም የጠፈር መንኮራኩር ወደ ሌላው እንደ ጭነት፣ የጨረቃ ናሙናዎችን ብሎም የሰው ልጅን ህዋ ላይ እንድታጓጉዝ ወይም እንድታስተላልፍ የሚያስችል መሆኑን አንድ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በህዋ ውስጥ ሮቦት ለመስራት፣ የጠፈር መንኮራኩሮች ቁጥጥርና ለወደፊት ተልእኮዎች አስፈላጊ መሆኑም ተነግሯል፡፡