አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተራ እና ጥምቀት በዓላት በድምቀት ተከብረው እንዲጠናቀቁ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ተግባር መግባቱን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ÷ በዓሉ በሚከበርባቸው ቦታዎች ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የስምሪት አቅጣጫን በመከተል ፀጥታ የማስከበር ተግባሩ ይከናወናል ብለዋል፡፡
በዓሉ ሐይማኖታዊና ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርም ከሐይማኖት አባቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውጤታማ ውይይቶች ተደርገዋል ማለታቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡
የበዓሉን ድምቀት ሊያበላሽ የሚችል ማንኛውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ድርጊትና እንቅስቃሴን የፀጥታ ኃይሉ እንደማይታገስም ነው ያስታወቁት፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው÷ ጃን-ሜዳ እና አቃቂ ቃሊቲ የታቦት ማደሪያዎችን ጨምሮ ሕዝብ በብዛት በሚታደምባቸው ባሕረ ጥምቀቶች ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎች ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በዓላትን እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወንጀል ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር ፖሊስ ከሚያከናውነው ግልፅና ሥውር ጥበቃ ባሻገር ሕብረተሰቡ አካባቢውን በመቆጣጠርና መረጃ በመስጠት ተባባሪነቱን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ሆነ ለሠላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ በ011-1-26-43-59 ፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ሕብረተሰቡ ጥቆማ መስጠት ይችላል ተብሏል፡፡