አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በኢንቨስትመንት እና በግብርናው ዘርፍ ያላቸውን ዘርፈ-ብዙ ትብብር ለማሳደግ ያለመ ምክክር ተካሄደ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በአዘርባጃን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያልቺን ራፊየቭ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ልዑኩ ከሚኒስትሩ ጋር በነበረው ውይይት ሀገራቱ በእንስሳት እና በሰብል ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በውኃና መሬት አጠቃቀም፣ በዲጂታል ግብርና፣ በቴክኖሎጂ አተገባበር፣ በግብርና ምርቶች ንግድ፣ በመስኖና በሌሎች የግብርና ልማት ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መክረዋል፡፡
ግብርና ለሀገሪቱ አጠቃላይ ዕድገት 1/3ኛ ድርሻ እንዳለው እና ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልከው እስከ 80 በመቶ ያህሉ ኤክስፖርት የግብርና ምርት መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በእንስሳት ቁጥር በአፍሪካ ቀዳሚ ብትሆንም ከዘርፉ የሚደረገው ኤክስፖርት ዝቅተኛ መሆኑንና የግብርና ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ በመላክ ረገድም ብዙ መሰራት እንዳለበት መጠቆማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ ልዑኩ ከኮሚሽነሩ ጋር ባደረገው ምክክር በኢትዮጵያ ስላሉ ዋና ዋና የኢንቨስትመንት አማራጮች እና ምቹ ሁኔታዎች ላይ ተወያይቷል፡፡
በዚሁ ወቅትም መንግሥት ባለፉት ዓመታት ያደረጋቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻዎች እና ለኢንቨስተሮች የሚያደርጋቸውን ድጋፎች ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡
ከምክክሩ በኋላም ልዑኩ በሀገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
ሁለቱም ወገኖች ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትብብር እንደሚሠሩ የተገለጸ ሲሆን÷ የሁለትዮሽ ኢንቨስትመንቶችን ለማሳለጥም የሕግ ማዕቀፉን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ተነስቷል፡፡
በሀገራቱ ኢንተርፕራይዞች መካከል ያለውን አጋርነት ለማሳደግም የቢዝነስ ዝግጅቶችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ መግበባት ላይ ተደርሷል፡፡