የሀገር ውስጥ ዜና

ሎስ አንጀለስ ተጨማሪ የእሳት አደጋ ሊያጋጥማት እንደሚችል ተጠቆመ

By Mikias Ayele

January 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሎስ አንጀለስ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ከባድ ነፋስ እንደሚኖር የትንበያ መረጃ ማመላከቱን ተከትሎ ተጨማሪ የእሳት አደጋ ሊያጋጥማት እንደሚችል ተጠቆመ፡፡

የአየር ንብረት ትንበያዎች እንደሚያመላክቱት በሎስ አንጀለስ ሰሜን ምዕራብ ክልል ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ከፍተኛ ነፋስ የሚኖር ሲሆን ይህም በግዛቷ ሌላ አስከፊ የእሳት አደጋ ሊያስከትል ይችላል ተብሏል፡፡

የአደጋውን ጉዳት ለመከላከል የእሳት አደጋ ሰራተኞች ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውም ተገልጿል።

ይሁን እንጂ ዝናብ የማይዘንብ ከሆነ የአደጋውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንደማይቻል ተመላክቷል፡፡

ባለፉት ቀናት በሰሜን እና ምዕራብ ሎስ አንጀለስ የተከሰተው ሰደድ እሳት 37 ሺህ ሄክታር ቦታ ማቃጠሉ የተገለፀ ሲሆን 35 በመቶ የሚሆነው የሰሜን ሎስ አንጀለስ ክፍል በእሳት አደጋ ሰራተኞች መትረፍ መቻሉ ተጠቁሟል፡፡

በቃጠሎ 25 ሰዎች መሞታቸውን የከተማዋ ሚዲካል ቡድን ሲያስታውቅ ከ250 እስከ 275 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ወድሟልም ነው የተባለው፡፡

በአሜሪካ ታሪክ አስከፊ በተባለው ሰደድ እሳት ከ150 ሺህ በላይ የሎስ አንጀለስ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸው ሲገለፅ ተጨማሪ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለማውጣት ጥረት እተደረገ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡