Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በትኩረት ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የአዘርባጃኑ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያልቺን ራፊዩቭ በጋራ የመሩት የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ሶስተኛ ዙር የፖለቲካ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት አምባሳደር ምስጋኑ÷ አዘርባጃን 29ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በተሳካ ሁኔታ በማስተናገዷ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል በመደበኛነት የሚካሄደው የፖለቲካ ምክክር ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን ያላቸውን ሁለንተናዊ ግንኙነት በግብርና፣ ማዕድን፣ ማኑፋክቸሪንግ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፎች የበለጠ እንዲጠናከር ያግዛል ብለዋል።

ያልቺን ራፊዩቭ በበኩላቸው ÷ በሀገራቱ መካከል የተካሄዱ የከፍተኛ መንግስት ስራ ኃላፊዎች ጉብኝቶች እያደገ የመጣውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አመላካች መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይቱ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እና የተፈረሙ ስምምነቶችም ተግባራዊ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥተውና ተቀራርበው ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version