የሀገር ውስጥ ዜና

የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት 16 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ

By Melaku Gedif

January 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ባለፉት 6 ወራት ከተለያዩ አገልግሎቶች 16 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በሰጡት መግለጫ ባለፉት 6 ወራት 10 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 16 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም 1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ቡክሌት ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ከ721 ሺህ በላይ ፖስፖርት ታትሞ መሰራጨቱን አስረድተዋል፡፡

መደበኛ ፓስፖርት (አዲስና እድሳት) 649 ሺህ 326 የተሰጠ ሲሆን÷ አስቸኳይ ደግሞ 71 ሺህ 372 መሰራጨቱን ነው የተናገሩት፡፡

በአጠቃላይ 721 ሺህ 623 ፖስፖርት የታተመ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 701 ሺህ 871 ወይም 98 በመቶ ተገልጋዮች ፓስፖርታቸውን እንደወሰዱ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለቱሪስት፣ ለኮንፍረንስና ለቢዝነስ የሚገቡትን በስፋት ለማስተናገድ 188 ሀገራት ቪዛ ኦን አራይቫል በመክፈት እየተሰራ መሆኑም አብራርተዋል፡፡

በዚህም በአየር ወደ ሀገር ለገቡ 1ሚሊየን 606 ሺህ 902፣ ከሀገር ለወጡ 1 ሚሊየን 240 ሺህ 210 እና ለሌሎች በድምሩ ለ3 ነጥብ 3 ሚሊየን መንገደኞች አገልግሎት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ከመከላከል ረገድም ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በንጅት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሕገ-ወጥ የድለላ ሥራዎች በተለያየ የማጭበርበርና የማታለል ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ አጠቃላይ 126 ተጠርጣሪዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ