Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን የምትልካቸውን ምርቶች ብዝኀነት ለማስፋት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን የምትልካቸው ምርቶች ብዝኀነትን ለማሳደግና ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኗን የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በአዘርባጃን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያልቺን ራፊየቭ ከተመራ ልዑክ ጋር የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጎልበት ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍትና እምቅ ዕድሎችን ለመለየት ያስቻለ ውይይት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን ከምትልካቸው ምርቶች መካከል ሰሊጥ፣ የተቆላ ቡና፣ ተልባ፣ የፍየል እና የበግ ሥጋን ጨምሮ ሌሎችም እንደሚገኙበት ሚኒስቴሩ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የላከው መረጃ አመልክቷል።

እንዲሁም ከአዘርባጃን በከፊል የተጠናቀቁ የብረት እና የቆርቆሮ፣ የሴንትሪፉጅ አካላት እና የኤሌክትሪክ ሰርኪዩቶችን የሚከላከሉ መሳሪያዎች ታስገባለች።

ኢትዮጵያ ወደ አዘርባጃን የምትልካቸው ምርቶች ብዝኀትን ለማሳደግና ለማስፋፋት ቁርጠኛ መሆኗን ሚኒስትሩ ለልዑኩ አረጋግጠዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ የግሉ ዘርፍ ግንኙነትን በማጠናከር፣ የቴክኖሎጂና የስልጠና ትብብር በማድረግና እና ልንገበያያቸው የምንችላቸው ምርቶችን በማስተዋወቅ ለማማሻሻል ተስማምተናል ብለዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ግንኙነታችንን ለማሳደግ ተጨማሪ ዕድሎችን መፈተሽ በሚያስችሉ ስልቶች ላይም መግባባት ላይ ደርሰናል ሲሉ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በቀጣይም ዝርዝር ስምምነቶችን በማድረግ የረጅም ጊዜ ኢኮኖሚያዊ አጋርነትን ለማጎልበት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

Exit mobile version