Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሁለንተናዊ ስርዓተ ምግብ ለመፍጠር እየተሰራ ነው – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሁለንተናዊ ስርዓተ ምግብ ለመፍጠር በጋራ እየተሰራ ነው ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ስርዓተ-ምግብ የአየር ንብረት ለውጥ ሊያደርስ ለሚችለው ተፅዕኖ ምላሽ መስጠት ላይ ትኩረቱን ያደረገ መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)÷ ለዓለም ስጋት እየሆነ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ በተለይ በዜጎች የአመጋገብ ስርዓት ላይ የከፋ ተፅዕኖ እንዳያደርስ ኢትዮጵያ በቅንጅት እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም መንግስት ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ የግሉን ዘርፍ ጭምር በማሳተፍ እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው÷ የስርዓተ ምግብ ላይ ትኩረቱን ያደረገው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ላይ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረው ተፅዕኖው በሁሉም ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

መድረኩ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ዙሪያ የሚከናወኑ ተግባራትን፣ የስርዓተ-ምግብ ሽግግር እና አመጋገብን ለማቀናጀት የሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶችን በማጣጣም ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተመላክቷል።

በተባበሩት መንግስታት የስርዓተ-ምግብ ማስተባበሪያ ማዕከል የሚመራው ኮንቨርጀንስ ኢኒሼቲቭ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ባለሙያዎችን፣ የተባበሩት መንግስታት ተወካዮችን እና ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን ትብብር በማጎልበት የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ እና የፓሪስ ስምምነት ትግበራን ለማሳለጥ ያለመ ነው ተብሏል።

በኢኒሼቲቩ 15 ሚኒስትሮች በቅንጅት እንደሚሠሩም ተመላክቷል።

መድረኩ ኢትዮጵያ በዘላቂ ልማት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የስርዓተ-ምግብ ለውጥ ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ለዓለም ለማሳየት እንደሚያግዝም ተጠቁሟል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ፣ መሳፍንት ብርሌ እና ሶስና አለማየሁ

Exit mobile version