የሀገር ውስጥ ዜና

በሸገር ከተማ የመሰረተ የልማት ችግር እየተባባሰ መምጣቱን ነዋሪዎች ገለጹ

By ዮሐንስ ደርበው

January 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸገር ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰቡን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት በከፍተኛ ሃላፊነት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሸገር ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ላይ ሰፊ ቅሬታ እንዳላቸው ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የመብራት አገልግሎት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

በሱሉልታ ከተማ የወሰርቢ ወረዳ ነዋሪዎች ላለፉት 3 ዓመታት የመንገድ ጥገና ሥራ እንዲከናወን ቢጠይቁም እስካሁን ምንም አይነት መፍትሄ እንዳላገኙ ነው የገለጹት፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች÷ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ዝርጋታ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

በዚህም በክረምት ወቅት በጭቃ፤ በበጋ ደግሞ በአቧራ መቸገራቸውን ጠቁመው÷ መንገዱ በፍጥነት ካልተሰራ ወጥተው ለመግባት እንደሚቸገሩ አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በአጭር ጊዜ ማግኘት ፈተና እንደሆነባቸው የተናገሩት ነዋሪዎቹ÷ ባለፉት 3 ዓመታት ምንም አይነት ቆጣሪ እንዳላገኙ አንስተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ በሱሉልታ ከተማ እምብርት እየኖሩ በዚህ ደረጃ በመሰረት ልማት እጦት መቸገራቸው እንዳሳዘናቸው አብራተዋል፡፡

የሱሉልታ ክ/ከተማ መዘጋጃ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደረጀ ያኢ በሰጡት ምላሽ÷ እስካሁን የደረሰን ቅሬታ የለም ብለዋል፡፡

የገፈርሳ ጉጄ፣ መልካ ኖኖ እና ኩራ ጂዳ ክ/ከተማ ነዋሪዎችም ተመሳሳይ የመሰረተ ልማት ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የሸገር ከተማ ማዘጋጃ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ነቢላ ኦሊ በበኩላቸው÷ በክፍለ ከተሞቹ የመሰረተ ልማት ችግር መኖሩን ጠቅሰው የሚስተዋሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እንሰራለን ብለዋል፡፡

የሸገር ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰቡን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት በከፍተኛ ሃላፊነት እየሰራ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በሲፈን መገርሳ