የሀገር ውስጥ ዜና

ሰው ተኮር ልማቶች መጎልበት እንዳለባቸው ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

January 15, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ማኅበራዊ ሰው ተኮር ልማቶች መጎልበት አለባቸው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር አስገነዘቡ፡፡

ፍትሕ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ በጋምቤላ ክልል በክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ-ግብር ከሦስት ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነቡትን የአቅመ ደካማ ቤት አስረክበዋል፡፡

በዚሁ ወቅት አፈ-ጉባዔው እንዳሉት÷ በተለይም ወጣቶችን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማስተባበር በማሕበረሰቡ ውስጥ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ማገዝ ይገባል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም የማሕበረሰቡ ባሕል መሆን ይገባዋል ማለታቸውን የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ናቸው፡፡

የበጎ ፈቃድ ሥራዎች አንድነትን የሚፈጥሩ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ዴዔታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በበኩላቸው ተቋማቸው እና ተጠሪ ተቋማቱ ከመደበኛ ተግባራት ባሻገር የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን እያከናወኑ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡