Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የግንዛቤ እጥረት መደበኛ ፍልሰትን ማባባሱ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር ውስጥ ሠርቶ ከመለወጥ ይልቅ በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ብቻ መለወጥ እንደሚቻል የሚያምኑ ዜጎች መበራከት እና የሕገ-ወጥ ደላሎች ቁጥር መጨመር መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት እንዲባባስ አድርጓል ተባለ፡፡

ባለፉት 6 ወራት ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ድንበር ላይ የተያዙ 1 ሺህ 239 መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ተጎጂዎች፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ የተመለሱ 31 ሺህ 358፣ ከየመን የተመለሱ 2 ሺህ 304 እና ከቤይሩት የተመለሱ 237 ወገኖች ማኅበራዊ አገልግሎት ካገኙ በኋላ ወደ ቤተሰብ መቀላቀላቸውን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ወደ ቤተሰብ ከመሄዳቸው በፊት በማዕከላት የጤና ምርመራ እና ክትትል እንደሚደረግላቸው በሚኒስቴሩ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ደረጄ ተግይበሉ ገልጸዋል፡፡

ወደ ቤተሰብ ሲሄዱም አልባሳት እና የትራንስፖርት ገንዘብ እንዲያገኙ መደረጉን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በወጣቱ፣ በወላጆች፣ በሕብረተሰቡ እና በደላሎች በኩል ዜጎች ውጭ ሀገር ካልሄዱ ሠርተው እንደማይለወጡ ማመን፣ በአጭር ጊዜ በርካታ ገንዘብ የማግኘት ፍላጎት ማሳየት እንዲሁም በሀገር ውስጥ በቂ የሥራ ዕድል የለም ብሎ ማመን ለሕገ-ወጥ ፍልሰቱ መባባስ ምክንያት መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ይህን ችግር ለመቅረፍ የግንዛቤ ፈጠራ እና ስልጠና መስጠትን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ዜጎች በውጭ ሀገር መሥራት ቢፈልጉ እንኳን በሕገ-ወጥ መንገድ በመሄድ ለዘርፈ-ብዙ ኪሳራ ከመጋለጥ ይልቅ÷ በሕጋዊ መንገድ የሚሄዱበት አሠራር እየተተገበረ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version