የሀገር ውስጥ ዜና

ጂኦ-ፖለቲካዊ ተግዳሮቶችን በማለፍ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል ተባለ

By Meseret Awoke

January 14, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2017 ዓ.ም የሥድስት ወራት ስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት አካሄደ።

በሪፖርቱ በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ ያስቻሉ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።

የባህር በር ጉዳይን አጀንዳ በማድረግ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ፍላጎትና ብሔራዊ ጥቅም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ ማድረግ ተችሏል።

ኢትዮጵያ መልካም ጉርብትና እና ሁለንተናዊ ግንኙነትን ከጎረቤት ሀገራት ጋር እንድታሳድግ ያስቻሉ ተግባራት መከናወናቸውም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት በአባልነት መመረጧ ባለፉት ስድስት ወራት ከተገኙ ስኬቶች አንዱ እንደሆነም ነው የተነሳው፡፡

በቀጣይም የአፍሪካ ህብረት ሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ለመሆን ፍኖተ-ካርታ ተቀርፆ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

ሚኒስቴሩ ሃብት በማፍራትና ሙያን መሰረት ያደረገ የሰው ሃይል ስምሪት በማድረግ የተሻለ ክንውን እንደነበረውም ነው ተገለጸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ፥ እየተተገበረ የሚገኘውን የተቋሙን የለውጥ ስራዎች በመፈተሽ በቀጣይ ሥድሰት ወራት ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው ፥ ባለፉት ሥድስት ወራት ውስጥ የተመዘገቡ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች በበርካታ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ውስጥ በማለፍ የተገኙ መሆኑን ተናግረዋል።