Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት እና ዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት እና ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በአውሮፓ ህብረት የሲቪል ጥበቃ እና የሰብአዊ ርዳታ ስራዎች ዳይሬክተር ጄኔራል ማሴይ ፖፑቭስኪ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር ካርል ስካው ከተመራ የጋራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በውይይታቸው ወቅት÷ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት እና ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎች ሰብአዊ ርዳታ በመስጠት እንዲሁም ከ1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን በማስተናገድ ስኬት ማስመዝገቧን ጠቅሰው ይህም ሀገሪቱ የተወሳሰቡ ሰብአዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት አመላካች መሆኑን ገልጸውላቸዋል፡፡

አጋር አካላት ለውጥ የሚያመጡት ሰፋ ያለ የልማት አጀንዳ ሲደግፉና ሲያራምዱ እንዲሁም ኢትዮጵያ ወደ ልማትና ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ሽግግር ሲያበረታቱ መሆኑንም አመልክተዋል።

የልዑካን ቡድኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሰብአዊ ድጋፍና ልማት ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት እና ቅንጅታዊ አሰራር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version