Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጎፋ በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች የማቋቋም ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጎፋ ዞን አስተዳደር ገለጸ፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዳግማዊ አየለ (ኢ/ር)÷ አደጋው የተከሰተበት ቀበሌን ጨምሮ በስጋት ቀጣና ውስጥ ያሉ 627 አባዎራዎችን በስድስት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች በማቆየት የምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ እርዳታ ሲደርሳቸው መቆየቱን ገልፀዋል።

የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተጎጂዎችን በመለየት 110 ቤቶችን በመገንባት ማስረከባቸውን ገልጸው 420 ቤቶችም እየተገነቡ መሆናቸውንና ቀጣይ የዝናብ ወቅት ሳይመጣ አጠናቅቆ ለማስረከብ ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡

ለመንደሮቹም የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ማሕበራዊ ተቋማትም አስፈላጊ መሆናቸው ታምኖበት የሰውና እንስሳት ጤና አጠባበቅ አገልግሎት ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የስነልቦና ማገገሚያ ማዕከላት መገንባታቸውን አብራርተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ጋንታ ጋምአ በበኩላቸው÷ በጎፋ ዞን በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ በአምስት ወረዳዎች ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውንና ወገኖችን በጊዜያዊና ቋሚነት የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት የደረሰበት የገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ነዋሪዎችን አስጊ ከሆኑ ቦታዎች በማውጣት በዘላቂነት ተደራጅተው እንዲኖሩ መንግስትና የተራድኦ ድርጀቶች እየተረባረቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የአደጋው ሰለባ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናትን ከሃዘን ተላቀው ጤናማ ማሕበራዊ መስተጋብር እንዲፈጥሩ ለማስቻል የተለያየ ሙያ እየሰለጠኑ የሚውሉባቸው ማዕከላት ማዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ሠለሞን ናቸው፡፡

በመለሰ ታደለ

 

Exit mobile version