አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ ዓመታት በተወሰዱ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ዕዳ ከሀገራዊ ጥቅል ምርት ያለውን ድርሻ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሯ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውጤቶችና ቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግሥት ከለውጡ በፊት የነበሩ የስርዓትና መዋቅራዊ ችግሮችን ለማስተካከል አዲስ የኢኮኖሚና ማህበራዊ የፖሊሲ ዕይታን መከተሉን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተተገበረው ፖሊሲ ኢኮኖሚውን ማዘመንና ለውድድር ክፍት ማድረግ ላይ መጠነ ሰፊ ሪፎርም መደረጉን ነው ያነሱት።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማና ትርፋማ ከማድረግ ባሻገርም በአዲሱ የፖሊሲ ዕይታ ለዓመታት ለግሉ ዘርፍ ዝግ የነበሩ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ግዙፍ ድርጅቶች ክፍት መደረጋቸውን አንስተዋል።
የመንግሥት ገቢን ከማሳደግ፣ የወጪ አስተዳደርን ከማስተካከል፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ የፕሮጀክት ትግበራና አፈጻጸምን ከማሻሻል፣ ድጎማን ለታለመለት ዓላማ ከማሸጋገር አንጻር አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውንም ጠቅሰዋል።
ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ ልማት ፋይናንስ የተደረገበት መንገድ ሀገር በዕዳ ቀንበር እንድትማቅቅ ያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ይህንን ለማስተካከል በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ምንም ዓይነት የንግድ ብድር ባለመፈጸም፣ ከአበዳሪዎች ጋር የዕዳ ሽግሽግ በማድረግና፣ ብድርን በከፍተኛ ሁኔታ በመክፈል የዕዳ ጫናውን ማቃለል ተችሏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ አሁን ያለባት የዕዳ ጫና ከሀገራዊ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ ከለውጡ በፊት ከነበረበት ከ30 በመቶ በላይ አሁን 13 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን አስታውቀዋል።
ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር፣ ገቢ፣ የወርቅና የቡና የውጭ ገበያ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል።