የሀገር ውስጥ ዜና

የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወነ ነው

By Meseret Awoke

January 14, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥምቀት በዓልን በድምቀት ለማክበር በቂ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያትን አስታወቀች፡፡

የቤተክርስቲያኗ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሊቀ ስዩማን እስክንድር ገ/ክርስቶስ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በጠቅላይ ቤተ-ክህነት ስራ አስኪያጅ የሚመራ የጥምቀት በዓል ዐብይ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚቴው በየዘርፉ ባሉ ንዑሳን ኮሚቴዎች አማካኝነት ጃንሜዳን ለበዓሉ ዝግጁ የማድረግ ብሎም የጸጥታ ስራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመስራት አጠቃላይ በዓሉን ለማክበር የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከሚመለከታቸው የመንግስት የጸጥታ አካላት ጋር ውይይቶች እየተደረጉ ለበዓሉ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡

ጃንሜዳን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከ200 በላይ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ላይ በዓሉ እንደሚከበር አንስተዋል፡፡

በማዕከል ደረጃ ያለውን ጨምሮ በሰንበት ትምህርት ቤቶች የጥምቀት በዓልን ታላቅነት የሚያሳዩ መዝሙሮች ጥናት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፥ የዘንድሮ ተረኛ አዘጋጅ ቤተ-ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ጥምቀት ፍጹም መንፈሳዊ በዓል በመሆኑ መከበር ያለበትም በመንፈሳዊ መንገድ ነው ያሉት ሊቀ ስዩማን እስክንድር፤ ምዕመኑ ከቤተክርስቲያኒቱ ማዕከላዊ አስተዳደር የሚተላለፉ መልዕክቶችን በማዳመጥ በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር በህግ ከተከለከሉ ነገሮች ሁሉ መራቅ አለበት ብለዋል፡፡

ምዕመኑም በዓሉን ከሚያውኩ ድርጊቶች ራሱን በማራቅ ሀይማኖታዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጃንሜዳን የማሳመርና የማስተካከል ስራው ከአንድ ሣምንት ቀደም ብሎ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፥ ስራውም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የከተራ ዕለት ጠዋት በጃንሜዳ መድረክ የማዘጋጀት ስራ የሚከናወን ሲሆን፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የመድረክ ስራውን ሙሉ ወጪ መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ