የሀገር ውስጥ ዜና

ጀርመን የኢትዮጵያ ታዳሽ የሃይል ልማት ሥራ አበረታች መሆኑን ገለጸች

By Melaku Gedif

January 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ሀንስ ሃንፊልድ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት÷ኢትዮጵያ ንጹህ የአረንጓዴ ኢነርጂ በማምረት ቀጣናውን በሃይል ለማስተሳሰር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ74 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡

የናይል ወንዝን ውሃ ሃብት በትብብር ከመጠቀም አንጻር የትብብር ማእቀፍ ስምምነቱ በ6 ሀገራት መጽደቁ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ያካተተ የውሃ ትብብር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡

ጀርመን በኢነርጂ ልማት ዘርፍ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በውሃ ሃብት አስተዳደር ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቁመው÷በተለይ ጂአይዜድ በገጠር የሀገሪቱ ክፍል ሃይል ለማዳረስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ከዋና የሃይል መስመር ርቀው የሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎችን የኦፍግሪድ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

አምባሳደር የንስ ሃንፊልድ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ ጥሩ እየሰራች መሆኑን አንስተው÷ የቀጣናዊ የሃይል ትስስሩ ዘርፈብዙ ትብበርን እንደሚያመጣ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተካሄደ ነው ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡