ቢዝነስ

ከውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር እየተዘጋጁ መሆኑን ባንኮች ገለጹ

By Melaku Gedif

January 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከውጭ ከሚገቡ ባንኮች ጋር ለመወዳደር አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የሀገር ውስጥ ባንኮች አስታወቁ፡፡

የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ በዘርፉ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው የባንክ ሥራ አዋጅ በቅርቡ መጽደቁ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም ፋና ዲጂታል ከውጭ የሚገቡ ባንኮች ጋር በዘርፉ ለመወዳደርና አቅማቸውን ለማሳደግ የሀገር ውስጥ ባንኮች ምን እየሰሩ ነው ሲል ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ÷ የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ እንዲሰማሩ የሚፈቅደው አዋጅ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ያስችላል፡፡

ንግድ ባንክ ከውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደርና ተመራጭ ለመሆንም አዳዲስ እና ዘመኑን የዋጁ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይም የአገልግሎት ጥራት፣ የዋጋ ተወዳዳሪነት እና የተሻለ ቴክኖሎጂን እውን ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

የውጭ ባንኮች የተሻለ ካፒታልና አገልግሎት ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል ያሉት አቶ አቤ÷ ለዚህም ባንኩ የካፒታል አቅሙን ከማሳደግ ጀምሮ ሁለንተናዊ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከቅርንጫፎች ጋር ተያይዞም በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ የባንኩን ቅርንጫፎች የማዋሃድ ሥራ መጀመሩን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የግሎባል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ ቦሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ባንኩ እንደ ሀገር የሚወጡ ሕጎችን ለመተግበር ሁሌም ዝግጁ ሆኖ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ከውጭ የሚገቡ ባንኮች ጋር በዘርፉ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል የባንኩ ሒደቶች ላይ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለዚህም ከፍተኛ የዘርፉ ባለሞያዎችን ያካተተ ኮሚቴ ተዋቅሮ ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችንና ሀገራዊ ሁኔታዎችን እያጠና ይገኛል ብለዋል፡፡

ከካፒታል ጋር ተያይዞም ብሔራዊ ባንክ የሚጠይቀውን 5 ቢሊየን ካፒታል እናሟላለን ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው÷ በቀጣይ ሁኔታዎች ላይ አዳዲስ ስትራቴጂዎች በመቅረጽ እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የፀሐይ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ መስፍን÷ ባንኩ በሀገር ውስጥ ከሚሰማሩ የውጭ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል አስፈላጊውን ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተለይም የካፒታል አቅምን ከማሳደግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ከመተግበር እና ከሌሎች ሁኔታዎች አንጻር ሰነድ ተዘጋጅቶ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባንኮቹ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሰሩ መፈቀዱ የፋይናንስ ተወዳዳሪነትን በማነቃቃት ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ