ዓለምአቀፋዊ ዜና

የእስራኤል ከፍተኛ የደህንነት ልዑክ በእስራኤል-ጋዛ ጉዳይ ለመወያየት ዶሃ ገባ

By Meseret Awoke

January 13, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የእስራኤል ከፍተኛ የደህንነት ልዑክ በእስራኤል-ጋዛ ጉዳይ ለመወያየት ኳታር ዶሃ መግባቱ ተሰምቷል፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቃል አቀባይ ፥ በሁለቱ አካላት ዙሪያ ስምምነት ሊደረስ ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

ኳታር፣ ግብፅ እና አሜሪካ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በአካባቢው ያለውን ጦርነት ለማስቆምና 98 ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡

የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱራህማን አልታኒ ጋር ባለፈው ቅዳሜ ከተገናኙ በኋላ ከኔታንያሁ ጋር መምከራቸው ተጠቁሟል፡፡

የእስራኤል እና የፍልስጤም ባለስልጣናት ከሐሙስ ጀምሮ በእስራኤል እና ሃማስ መካከል በተካሄደው ድርድር ላይ መጠነኛ መሻሻል ታይቷል ቢሉም ዝርዝር መግለጫ ግን አልሰጡም።

በቀደሙት የውይይት መድረኮች ከታዩ ትላልቅ ክፍተቶች መካከል ሀማስ ጦርነቱ እንዲያበቃ ሲጠይቅ እስራኤል ደግሞ ሃማስ ጋዛን እስካስተዳደረ ድረስ ጦርነቱን አላቆምም ማለቷ ያስታወሰው የሬውተርስ ዘገባ ነው።