አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ሁለት ተጨማሪ የዩክሬን መንደሮችን መቆጣጠሩን አስታውቋል፡፡
መንደሮቹ በምስራቅ ዶኔትስክ ግዛት የምትገኘው ያንታርን እና የሰሜን ምስራቅ ካርኪቭ ግዛቷ ካሊኖቭ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ጥቃቱ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አጋሮቻቸው ወደ ኪየቭ ሊልኩ ቃል የገቡትን ጦር መሳሪያ እንዲያደርሱ መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው የተፈጸመው ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ወታደሮች ከኩራኮቭ በስተደቡብ ምዕራብ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምስራቃዊ ዶኔትስክ ግዛት የሆነችውን ያንታርን መንደር መያዙን አስታውቋል።
በተጨማሪም የሩሲያ ወታደሮች በሰሜን ምስራቅ ካርኪቭ አካባቢ የካሊኖቭን መንደር መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
የክሊኖቭ መንደር በኦስኪል ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ ላይ እንደምትገኝ አልጀዚራ በዘገባው አስፍሯል፡፡
የሩሲያ ሃይሎች ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ በምዕራቡ ዳርቻ ድልድይ መስራታቸው የተገለጸ ሲሆን÷ ወንዙን ለመሻገርም ብዙ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተጠቁሟል፡፡