አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሃይማኖት ተቋማት የሕዝብ አብሮነት እንዲጎለብት ያላቸውን ሚና ይበልጥ እንዲያጠናክሩ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ጠየቁ፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ከጋምቤላ ከተማ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያይተዋል።
በመድረኩ የተገኙት ወ/ሮ ዓለሚቱ እንደተናገሩት÷ሕገ መንግስቱ የእምነት ነፃነትን ያከበረና ዜጎች የፈለጉትን እምነት የመከተልና የማስፋት ሙሉ መብትን ያጎናፀፈ ነው።
ሕገ-መንግሥቱ ለዜጎች ባጎናፀፈው መብትም የህዝቦች አንድነትና አብሮነት ይበልጥ እንዲጠናከር ዕድል የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት በሥነ-ምግባር የታነፀ ዜጋን በማፍራት ለክልሉ ብሎም ለሀገር ሰላም የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ዘመናትን የተሻገረውን የሃይማኖቶች እኩልነትንና መቻቻልን ይበልጥ በማጠናከር ለአካባቢው ሁለንተናዊ ሰላምና ልማት ሁሉም በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በህዝቦች መካከል ያለውን አብሮነትና አንድነት ይበልጥ በማጎልበት ረገድ የእምነት ተቋማት አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ይህን ሚናቸውም ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው÷ ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር በመተባበር ለሀገር ሰላምና ልማት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ አሁን ላይ የተገኘውን ሰላም በማፅናት ረገድ ከእምነቱ ተከታዮች ብዙ እንደሚጠበቅ አጽንኦት መስጠታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡