Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአማራ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በክልሉ በተውለደሬ እና ሀይቅ ከተማ ከ94 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በዛሬው እለት ተመርቀዋል፡፡

አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ የክልሉ መንግስት ለንጹህ መጠጥ ውሃ ስራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ዛሬ ወደ ስራ የገቡት ፕሮጀክቶች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ማህበረሰቡም የሚሰሩ የመጠጥ ውሃ ግንባታዎች በዘላቂነት እንዲያገለግሉ መጠበቅ እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) 78 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የሀይቅ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት 56 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር እንደወጣበት ገልጸዋል፡፡

21 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የቆርኬና የበደዶ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ደግሞ 38 ሚሊየን ብር ወጪ እንደተደረገበት አመልክተዋል።

በከድር መሀመድ

Exit mobile version