አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ክልሎች ከአዲስ አበባ ባገኙት ተሞክሮ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሻሻል በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የክልልና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ዘርፍ ተቋማት የአዲስ አበባ የተሞክሮ ልውውጥ ጉብኝት ማጠቃለያና የ”መንገድ ለሰው” ንቅናቄ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷በአዲስ አበባ ከተማ እና እንደ ሀገር እየተተገበረ ያለው የለውጥ ስራ ለትራንስፖርት ዘርፉ መልካም አጋጣሚን የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ በትራንስፖርት ዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን እንደፈታ ጠቅሰው÷ከመንገዶች መስፋት በተጨማሪ የተለየ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ መሰራቱ ምቹ የከተማ ትራንስፖርት ፍሰት እንዲኖር አድርጓልም ነው ያሉት፡፡
የክልል ትራንስፖርት ቢሮዎችም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ዘርፍ ተቋማት የወሰዱትን ተሞክሮ በተግባር በማዋል ጊዜን፣ ጉልበትንና ገንዘብን የሚቆጥብ አገልግሎት ማቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
መንገዶችን ከተሽከርካሪ ነፃ በማድረግ የሚካሄደው ሳምንታዊ “የመንገድ ለሰው” ንቅናቄ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን ከማበረታታት በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መገለፁን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡