አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና የቻይና 55ኛ የወዳጅነት በዓል በወዳጅነት አደባባይ እየተከበረ ነው፡፡
በመርሐ ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቸን ሃይ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በመድረኩ÷የ55ኛ የወዳጅነት ክብረ በዓል በሁሉም መስኮች እየተጠናከረ ለመጣው የኢትዮጵያ እና የቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳያ ነው ብለዋል።
ቻይና የኢትዮጵያ ዋነኛ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አጋር መሆኗን ገልጸው የሀገሪቱ ባለሃብቶች መንግስት ያመቻቸውን አስቻይ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
አምባሳደር ቺን ሃይ በበኩላቸው÷የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት በጊዜ እና በሁኔታዎች መቀያየር የማይለወጥና ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን አስረድተዋል።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ መስኮች አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች በሁለቱም ሀገራት ቡድኖች ቀርቧል፤እንዲሁም ገቢው ዲቦራ ፋውንዴሽንን ለማጠናከር የሚውል የተለያዩ ምርቶች የቀረቡበት ባዛር ለህዝብ ክፍት ሆኗል፡፡
በወንደሰን አረጋኸኝ