አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ወረዳ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና በህብረተሰቡ ላይ ችግር ሲፈጥሩ የቆዩ ቡድኖች የመንግስትን የሠላም ጥሪ በመቀበል እጃቸውን እየሠጡ እንደሚገኙ ተገለፀ፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ከአካባቢው የፀጥታ ሀይል ጋር በመቀናጀት ባደረገው የሚያቋርጥ ስምሪት በፅንፈኛው ቡድን ላይ ተከታታይ ርምጃ በመወሰዱ አካባቢው የሰላም ቀጠና ሊሆን መቻሉን የሰሜን ጎንደር ዞን ኮማንድ ፖሰት ሰብሳቢ ሜጄር ጄኔራል አማረ ገብሩ አሥረድተዋል።
ህብረተሠቡም ሰለሰላም በመምከር በተሳሳተ አጀንዳ ወደ ፅንፈኛው ቡድን የተቀላቀሉት ወደ ሠላም እንዲመለሱ ሠፊ ሥራ መሥራቱን የገለፁት ጄኔራል መኮንኑ አሁንም በተሳሳተ መንገድ ጫካ የሚገኙትን መምከርና ወደ ሠላም መመለስ እንደሚገባ አመላክተዋል።
ወደ ሠላም የተመለሱ ታጣቂዎች በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ተታለው ወደ ጫካ እንደገቡ ገልፀው ህዝብን ለመካስ ከፀጥታ ሃይሉና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ ማረጋገጣቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡