አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ በርዋንዳ መዲና ኪጋሊ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ጎበኘ፡፡
በጉብኝቱ ልዑኩ በኪጋሊ ያለውን የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የከተማ ጽዳትና ቆሻሻ አወጋገድ፣ የአስተዳደር አገልግሎቶችን ተደራሽነትን ለማሻሻል እንዲሁም በህዝብ ትራንስፖርት የዲጅታል ክፍያ ስርዓትን ተመልክቷል፡፡
ከጉብኝቱ በተጨማሪ ልዑኩ የኪጋሊ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ ከከተማው አመራር አባላት ጋር የመንገድ መሠረተ ልማት፣ የቤት አቅርቦት፣ የቆሻሻ አወጋገድ፣ የአካባቢ ጽዳትና የከተማ አረንጓዴ ልማትን በተመለከተ ውይይት አድርጓል፡፡
በጉብኝቱ አቶ ሽመልስ በኪጋሊ የተመለከቷቸው የቤቶች መልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች ለከተማዋ ውበት ከመጨመር ባለፈ የነዋሪውን የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻላቸውን እንደተመለከቱ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ልዑኩ በኪጋሊ በኒያሩታራማ የሚገኘውን የኪጋሊ ጎልፍ ሪዞርት እና ቪላዎችን መጎብኘቱን የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡