የሀገር ውስጥ ዜና

በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

By Mikias Ayele

January 11, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካን የምግብ ሉዓላዊነት እና ዕድገትን ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለፁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በኡጋንዳ ካምፓላ እየተካሄደ ባለው በመሪዎች ደረጃ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ፕሮግራም (ካድፕ) አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ግብርና ልማት ፕሮግራም ሻምፒዮን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ወክለው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ከድህረ ማላቦ ፕሮግራም በኋላ በካምፓላ የተዘጋጀው የካድፕ ስብሰባ የአህጉሩን ግብርና እና ስነ ምግብ ስርዓት ፈትሾ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለማዘጋጀት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡

የአፍሪካ ምግብ ስርዓትን ለማረጋገጥ የአህጉሩን ኢኮኖሚ፣ ስነ ሕዝብ፣ ቴክኖሎጂ፣ አካባቢያዊ እና አየር ንብረት ሁኔታዎች ታሳቢ ባደረገ መልኩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና ውጤቶች መመዘገባቸውን ገልፀዋል፡፡

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ባለድርሻ አካላት የአፍሪካ ምግብ ስርዓትን በተመለከተ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በመገንዘብ፣ ችግሮችን በመረዳት እና ጥሩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በአፍሪካ አስተማማኝ የምግብ ስርዓትን ለማረጋገጥ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በአፍሪካ ከተሜነትን ማስፋፋት፣ የሴቶችን እና ወጣቶችን አቅም ማጎልበት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራን ማጠናከር እና እንደ ነፃ የንግድ ቀጣና አይነት ፖሊሲዎችን መተግብር እንደሚስፈልግ አብራርተዋል።

በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት እና ዕድገትን ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት ስለሚያስፈልግ ድንበር ተሻጋሪ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡