አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከ305 ሺህ በላይ ጎብኝዎች ጉብኝት ማድረጋቸውን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
በእነዚህ ጎብኝዎች ምክንያትም በቱሪዝም ሴክተሩ ከ488 ሚሊየን ብር በላይ ቀጥተኛ ያልሆነ ገንዘብ መንቀሳቀሱን የቢሮው ኃላፊ ሳሙኤል መንገሻ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ በቱሪዝም ሴክተሩ ይንቀሳቀሳል ተብሎ የታቀደው 556 ሚሊየን ብር እንደነበር አስታውሰው÷ የዕቅዱን 92 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
አልፎ አልፎ የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች፣ ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም መስኅቦችን ከማስተዋወቅ አንጻር፣ ከቱር ኦፕሬተሮች እና አስጎብኝዎች ጋር ጠንካራ ቅንጅት አለመኖር ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን አንስተው÷ እነዚህን ውስንነቶች ለመፍታት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም የመዳረሻ ልማት ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው