አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት ከአራት የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች 353 ነጥብ 41 ጊጋ ዋት ሠዓት ማመንጨት መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በግማሽ ዓመቱ በአጠቃላይ ከመነጨው ውስጥም የነፋስ ኃይል ማመንጫ ድርሻ 2 ነጥብ 6 በመቶ መሆኑን በጄነሬሽን ኦፕሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት የፕላኒንግ ሥራ አስኪያጅ ጥሩወርቅ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት አዳማ አንድ 65 ነጥብ 41፣ አዳማ ሁለት 182 ነጥብ 22፣ አይሻ ሁለት 91 ነጥብ 31 እንዲሁም አሸጎዳ 14 ነጥብ 2 ጊጋዋት ሠዓት ኃይል ማመንጨታቸውን ነው ለፋና ዲጂታል የተናገሩት፡፡
የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ከሌሎች ኃይል ማመንጫዎች አንጻር ካላቸው የተለየ ጥቅም አንዱ÷ የዝናብ እጥረት ወይም ድርቅ ቢከሰት በችግሩ ተጽዕኖ ውስጥ ሳይወድቁ በዘላቂነት ኃይል ማመንጨት መቻላቸው ነው ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው