Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፀጥታ ሁኔታን ለመቆጣጠር የድሮኖች ስምሪት ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፀጥታ ጥምር ኃይል በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ያለውን የፀጥታ ሁኔታን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፤ የወንጀል መከላከል ሥራችንን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ የሚችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በቅርብ ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ ፍሰትና አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም ታላላቅ ፕሮግራሞችን ቁጥጥር ማድረግ የሚችሉ የድሮኖች ስምሪት ይደረጋል ሲሉም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ደህንነት ዘላቂ እንዲሆን የፀጥታ ጥምር ኃይሉ ተቀናጅቶ በመሥራቱ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በዚህም አሁን ላይ በአዲስ አበባ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ ያለበትና በቀጣይ በሀገራችን የሚከበረው የጥምቀት በዓል እና የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በሰላም እንዲጠናቀቁ ከወዲሁ ይህንን የሚመጥን ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ አልፎ አልፎ የሚገጥሙ የተሽከርካሪ እቃዎችና የሞባይል ስርቆቶች የሚስተዋሉ ስለሆነ ህዝቡ እና ቱሪስቶች ያለ ስጋት በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ ችግሮቹን ለማስወገድ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በከተማዋ ወንጀል መቀነስ የተቻለው በቀንና በማታ የቴክኖሎጂ አቅሞችን በመጠቀም ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከመላው ህብረተሰብ፣ ከሰላም ሰራዊት እና ከደንብ አስከባሪዎች ጋር በቅንጅት በመሰራቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የሽብር ኃይሎች ፀጥታ ለማደፍረስ በተለያየ መንገድ ያደረጉትን ሙከራ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በተቀናጀ መንገድ ማክሸፉን ማስታወሳቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል።

የከተማዋ ፀጥታ እጅግ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡

Exit mobile version