የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የሙከራ የገንዘብ ገበያው ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ እንቅስቃሴ ተካሂዶበታል – ጠ/ሚ ጽ/ቤት

By Feven Bishaw

January 10, 2025

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የሙከራ የገንዘብ ገበያው ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ እንቅስቃሴ ተካሂዶበታል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ (ESX) መርቀው ከፍተዋል።

የጽህፈት ቤቱ መረጃ እንዳመለከተው፤ የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ተግባር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ በማዘመን ረገድ ዐቢይ ርምጃ ነው።

የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ለዘርፉ ግልፅነትን የተላበሰ የገበያ ስፍራ ይፈጥራል ያለው መረጃው፤ የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጥላ ሥርም በኢንቨስትመንት ለሚመራ እድገት በር ይከፍታል ብሏል።

የኢትዮጵያ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመንግሥትም በግልም ዘርፎች የፋይናንስ አካታችነትን በማስፋት የቁጠባ እንቅስቃሴን ማሳደግን ብሎም ኢንቨስተሮችን መጠበቅን ታላሚ አድርጎ መነሳቱን ገልጾ፤ በሶስት የገበያ ክፍሎች ላይ ይሰራል ሲል አመልክቷል።

እነዚህም ለቢዝነስ ተቋማት፣ ለመንግሥት እና ሌሎች ተቋማት የሚያገለግሉ የይዞታ ገበያ፣የቋሚ ገቢ ገበያ እና የገንዘብ ገበያ ናቸው ተብሏል።

የሙከራ የገንዘብ ገበያው ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ እንቅስቃሴ ተካሂዶበታል ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ፤ ይኽም ገበያው የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓት ለማጠናከር ብሎም ለዘላቂ ልማት የካፒታል አቅም ለማሰባሰብ ያለውን አቅም አሳይቷል ሲል ጠቅሷል።