የሀገር ውስጥ ዜና

ሠራዊቱ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው ተደርጓል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

By Feven Bishaw

January 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር መከላከያ ሠራዊት አካታች እንዲሆን በማድረግ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው ተደርጓል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

ተቋሙ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ የሠራዊት አደረጃጀት እና ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው አባላት የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማስከበር መከታና ኩራት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሰላም አማራጭ ቅድሚያ የሚሰጠውና የሀገርን ልማት ከዳር ለማድረስ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ይህንን በመጻረር የሚንቀሳቀሱ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ሽፍታዎች ላይ ሠራዊቱ ህግ የማስከበር እርምጃ የመውሰድ ህገ መንግስታዊ ኃላፊነት እንዳለበት አስታውሰዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው፥ ተቋሙ የተለያዩ የሠራዊት አደረጃጀት እና ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ሠራዊቱ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ አካታች እንዲሆን በማድረግ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው ተደርጓል ብለዋል።

ከለውጡ በፊት የነበረው ሠራዊት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ የተጫነበት እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ከየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እና እምነት ነጻ በማድረግ ሙያውን መሰረት ያደረገ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ሰላም የሚጠብቅ ሆኖ ተቋቁሟል ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህም የሚያፈነግጥ ሠራዊትና አመራር ካለ በህግ ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋቱንም መናገራቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ አመላክቷል።