የሀገር ውስጥ ዜና

አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን የስንዴ ድጋፍ ተደረገ በሚል ያሰራጩት ዘገባ ስህተት ነው- አገልግሎቱ

By Feven Bishaw

January 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ሰሞኑን ለስደተኞች የተደረገውን የስንዴ ድጋፍ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት እንደተደረገ በማስመሰል የተሳሳተ መረጃ ማሰራጨታቸውን ከስደት ተመላሾች አገልግሎት አስታወቀ፡

ሩሲያ ሰሞኑን የስንዴ ድጋፍ ያደረገችው ለተጠለሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች እንጂ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አለመሆኑን አገልግሎቱ አስገንዝቧል፡፡

ኢትዮጵያ ከ26 ሀገራት የመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን አስጠልላ ከለላን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በአግባቡ እየሠጠች መሆኗንም ነው ያስታወቀው፡፡

አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ መሰረት በስደተኞች ስም የሚመጣ ማንኛውም ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሠራ ነው፡፡

ሰሞኑንም በደቡብ ሱዳን ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡና በጋምቤላ ክልል ለተጠለሉ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ሩሲያ 1 ሺህ 632 ነጥብ 4 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ድጋፍ ማድረጓን ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ እውነታው ከላይ የተገለጸው ሆኖ ሳለ፤ ድጋፉ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት እንደተደረገ በማስመሰል የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ የመገናኛ ብዙኃን እንዳሉ ገልጿል፡፡

እነዚህ መገናኛ ብዙኃን እውነቱን መዘገብ እንዳለባቸው አስገንዝቦ÷ ለሠሩት ስህተት እርምት እንዲወስዱ አገልግሎት አሳስቧል፡፡