የሀገር ውስጥ ዜና

ትናንት ምሽት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ስለታዩት ተቀጣጣይ ቁስ አካላት …

By Melaku Gedif

January 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2016 (ኤፍ ኤም ሲ) ትናንት ከምሽቱ 1፡30 ገደማ በደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች በሰማይ ላይ እየተቀጣጠሉ በከፍተኛ ፍጥነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የቁስ አካላት ስብስብ መታየታቸው ይታወቃል፡፡

ለመሆኑ እነዚህ በሰማይ ላይ የታዩት ተቀጣጣይ ቁስ አካላት ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

በኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት የአስትሮኖሚና አስትሮ ፊዝክስ ተመራማሪ ገመቹ ሙለታ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ትናንት ምሽት ሰማይ ላይ ሲንቀሳቀስ የታየው ተቀጣጣይ ቁስ አካል በሁለት መንገድ ሊገመት ይችላል፡፡

አንደኛው መላምት ተፈጥሯዊ የሰማይ አካል ሊሆን እንደሚችል እና ሌላኛው ደግሞ ሰው ሰራሽ ቁስ አካል ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

እነዚህ ቁሶች በመሬት ስበት ውስጥ ሲገቡ በከባቢ አየር ሰበቃ ምክንያት እንደሚቃጠሉ የሚናገሩት ተመራማሪው÷ በዚህ ወቅትም ቃጠሎው እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡

አስትሮይድን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊ የሰማይ አካላት የሚባሉት በብዛት በማርስና በጁፒተር መካከል እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

እነዚህ አካላትም ልክ እንደ መሬት ጸሃይን ይዞራሉ፤ በዚህ ወቅትም በአጋጣሚ በመሬት ስበት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ነው ያብራሩት፡፡

በዚህ ወቅትም በመሬት ከባቢ አየር ሰበቃ ምክንያት ውጫዊ አካላቸው ይቃጠልና እሳት እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

ውስጣዊ አካላቸው ደግሞ በብረት ወይም ሲልኬት የተሞላ በመሆኑ መሬት ላይ ሊደርስ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

ሰው ሰራሽ አካል ከሆነ ደግሞ ህዋ ላይ የሚንቀሳቀሱ ነገሮች ሊኖሩ ስለሚችሉ ወደ ከባቢ አየር ውስጥ ሲገቡ የመቃጠል እና ተሰባብሮ የመውረድ ምልክቶችን እንደሚያሳዩ አስገንዝበዋል፡፡

ስለሆነም ክስተቱ በቤተ ሙከራ ተጠንቶ ወይም በባለሞያዎች በዘርፉ መሳሪያ ታይቶ እስካልተረጋገጠ ድረስ አስትሮይድ ነው ወይም ሰው ሰራሽ አካል ነው ብሎ መደምደም እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ