አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)ጄምስ ሆዌልስ የተባለ ቀደምት የክሪፕቶከረንሲ አልሚ ሰው ሰሞኑን ፍርድ ቤት የሚወሰድ ጉዳይ አጋጥሞታል።
ሰውየው “በዌልሷ ኒውፖርት ከተማ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ላይ በስህተት የተጣለ ንብረቴን እንድፈልግ ይፈቀድልኝ” የሚል ጥያቄ ለከተማ አስተዳደሩ አቅርቦ መልስ የሚሰጠው አካል በማጣቱ አቤቱታውን ወደ ፍርድ ቤት ወስዷል።
ፍርድ ቤቱም የሰውየውን ጉዳይ መርምሮ ለፍርድ ክርክር መቅረብ የማይችል ጉዳይ ነው በሚል ውድቅ አድርጎበታል።
ከቆሻሻ ጋር ተሰብስቦ ወደ ማስወገጃ ቦታ የተወሰደበት ንብረቱ ደግሞ በአሁናዊ ግምት 598 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ቢትኮይን የያዘ የክሪፕቶከረንሲ ዋሌት እንደሆነ ይናገራል።
ጄምስ እንደሚለው÷ እ.ኤ.አ በ2013 ጓደኛው በስህተት ቢትኮይን የተጠራቀመበትን ዋሌት የያዘ ቋት (ፍላሽ ድራይቭ) ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ እንደጣለበት ገልጿል።
ንብረቱን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን ቆሻሻ ክምር ውስጥ ለመፈለግ እንዲፈቀድለት ያቀረበው ጥያቄ በኒውፖርት ከተማ ፍርድ ቤት “ሊተገበር የማይችልና አሳማኝነት የሌለው” በማለት ውድቅ ተደርጎበታል።
ጄምስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ “በጣም የሚያበሳጭ” ሲል ገልጾ ለክርክር ቀርቤ ሃሳቤን እንኳ እንዳስረዳ እድል የሚነፍግ ድርጊት ሲል ወቅሷል።
ላለፉት 12 ዓመታት ለከተማው አስተዳዳሪዎች እየተመላለሰ ያቀረባቸው ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ውድቅ እንደተደረጉበት የተናገረው ጄምስ የገንዘቡን 10 በመቶ ለኔውፖርት ከተማ ማህበረሰብ ለመስጠትም ጭምር ተስማምቶ እንደነበር ጠቅሷል።
የከተማ አስተዳደሩን ወክሎ የተከራከረው ጠበቃ በበኩሉ ÷ማንኛውም ቆሻሻ ማከማቻ ቅጥር ግቢ ውስጥ የገባ ዕቃ፣ የከተማ አስተዳደሩ ንብረት እንደሚሆን ህግ ይፈቅዳል ሲል ተከራክሯል።
የቢትኮይን ዋጋ በ2024 ብቻ ከ80 በመቶ በላይ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 103 ሺህ 332 ዶላር ወይም 13 ሚሊየን ብር ገደማ በመድረስ በታሪክ ከፍተኛው ጭማሪ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል።
ቢትኮይን 55 ነጥብ 2 ከመቶ የክሪፕቶከረንሲ ገበያ ድርሻን የተቆጣጠረ የድጂታል ገንዘብ ነው።
በአሁኑ ወቅት 598 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው የጄምስ ሆውልስ ቢትኮይን በቀጣዩ ዓመት 1 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ሊኖረው እንደሚችል መገመቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆሞ ለማውረድ ያስቸግራል እንዲሉ እንደ ቀልድ ከቆሻሻ ጋር የተጣለ ንብረት የፍርድ ቤት ቢፈቅድ እንኳን ከሳር ክምር ውስጥ መርፌ እንደመፈለግ የሚከብድ ይመስላል።