የሀገር ውስጥ ዜና

በቀን 30 ሚሊየን ሊትር ፍሳሽ የሚያጣራ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ተመረቀ

By Feven Bishaw

January 10, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቀን 30 ሚሊየን ሊትር ፍሳሽ የማጣራት አቅም ያለው የቦሌ አራብሳ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል::

ማጣሪያ ጣቢያው የከተማዋን የፍሳሽ ማጣራት አቅም ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት በቀን 48 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ወደ 233 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ከፍ ማድረግ ማስቻሉን ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ገልፀዋል፡፡

ይህ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ከ240 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካባቢውን ነዋሪዎች የዘመናዊ ፍሳሽ ማጣሪያ ስርዓት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንዲሁም የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓትን የሚያዘምን፣ ለነዋሪዎች እና በአጎራባች አካባቢዎች ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የረዥም ጊዜ ቅሬታ ምላሽ የሚሰጥ፣ ከተማዋን ከብክለት የጸዳች፣ ውብ እና ምቹ ለማድረግ የተጀመረውን ስራ እዉን የሚያደርግ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡