የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ለወጣቶች ከ100 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል ተፈጠረ

By Feven Bishaw

January 10, 2025

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ለወጣቶች 125 ሺህ 212 የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ 100 ሺህ 682 ማሳካቱን የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ሰለሞን አየለ እንደተናገሩት፤ በግማሽ ዓመቱ ለወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል 18 ሺህ 944 ቋሚ እንዲሁም 81 ሺህ 738 ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

በክልሉ ባሉ ሁሉም ዞኖች የሚገኙ ወጣቶች በግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው እንዲሰሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቁመዋል።

በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ለተሰማሩ ወጣቶች የማምረቻ ቦታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ የተለያዩ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አመልክተዋል።

ወጣቶቹ የቁጠባ ባህልን በማዳበር በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የብድር አቅርቦቶችን በማመቻቸትና ውጤታማነታቸውንም በማረጋገጥ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በክልሉ ክህሎት መር የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ ለፋና ዲጂታል የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ ለዚህም የክልሉ ሙያና ቴክኒክ ስልጠና ተቋማትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአድማሱ አራጋው