Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያና ብራዚል በግብርና ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ከብራዚል የማህበራዊ እድገት፣ የቤተሰብ ድጋፍና የድህነት ቅነሳ ሚኒስትር ዌሊንግተን ዲያስ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ኢትዮጵያና ብራዚል በግብርና እና በምግብ ዋስትና መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

አምባሳደር ልዑልሰገድ÷በኢትዮጵያ ግብርናን የማዘመን፣ የምግብ ሉዓላዊነትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን እና የተመዘገቡ ውጤቶችን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡

ዌሊንግተን ዲያስ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተገኙ ውጤቶች ትምህርት እንደሚወሰድባቸው አንስተዋል፡፡

ብራዚል ድህነትን በመቀነስና ረሃብን በመዋጋት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸው÷ በድህነት ቅነሳና ረሃብን በመዋጋት በሚደረጉ ተግባራት በትብብርና በቅርበት እንሰራለን ብለዋል።

ሁለቱ ወገኖች በግብርና እና በምግብ ዋስትና መስክ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version