Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ደረጃ በደረጃ መፍታት ይገባል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘው ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ደረጃ በደረጃ መፍታት እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

በክልሉ “ከቃል እስከ ባህል”በሚል መሪ ሃሳብ ለተከታታይ አራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ወቅታዊ የውይይት መድረክ ተጠናቅቋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በሰጡት የስራ መመሪያ ÷ ከምንም ጊዜ በላይ አመራሩ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ፕሮጀክቶችን አቅዶ በአጭር ጊዜ በጥራትና ፍጥነት ተግብሮ ወደ ስራ በማስገባት እና ቃልን በተግባር በመለወጥ ፓርቲው በአንደኛው ጉባኤው የገባቸውን ቃሎች በተጨባጭ ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

በክልሉ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን በመግለጽ የተመዘገቡ ስኬቶችን በውጤት አጅቦ ማስቀጠል ከሁሉም አመራር የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ በማጎልበት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዘው ከህዝቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ደረጃ በደረጃ መፍታት እንደሚገባም ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል የግብርና ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በክልሉ ተግባራዊ እየሆኑ የሚገኙ የልማት ንቅናቄዎችን በማስቀጠል እያንዳንዱ አመራር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የተስተዋሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ መገለጹን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

 

 

 

Exit mobile version